በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራ

በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ኢንተርኘራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ከሰኔ 12-16 /2015 ዓ/ም ድረስ የሚቆይ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ።ኤግዚቢሽንና ባዛሩ “ኢትዮጵያ ታምርት”ንቅናቄና የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርት አገልግሎት ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ ነው።የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ ሚልክያስ ብትሬ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን ከፍተዋል።በዚህ ወቅትም አቶ ሚልክያስ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዚህ ባዛር መሳተፋቸው እርስ በርስ ከመተዋወቅ፣ ከመደጋገፍና ልምድ ከመለዋወጥ በተጨማሪ ምርቶቻቸው ለገበያ ከማቅረብ አኳያ የጎላ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል።አቶ ሚልክያስ አክለውም ለገበያ የቀረቡ ምርቶች የፈጠራ ስራ የታከለበት፣ጥራት ያላቸው፣ የውጭ ምርቶችን የሚተኩና ለሀገር ፋይዳ ያላቸው እንደሆኑ ጭምር ገልጸዋል።ምርቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረቡ በመሆኑ ዋጋን ከማረጋጋት አንጻርም ትልቅ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል። ከቦታ ማስፋፍያና ከማሳያ ቦታ ጋር ተያይዞ የቀረቡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ ይሆናል ነው ያሉት አቶ ሚልክያስ።የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሀላፊ አቶ ታምሩ ኡቴ ባዛሩ እንደ ሀገር በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ያለውን ተከትሎ በዘርፋ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዚህ ባዘር ተገኝተው ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ እንዲያስተዋውቁም ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።ነባሮችን በማጠናከር አዳዲሶችን በማካተት የፈጠራ ስራዎችን በማከል ጭምር ውጤት የታየበትም ነው ሲሉ አክለዋል።በተለይም በእንጨትና ብረታብረት ፣በቆዳ ምርት ውጤቶች የውጭ ምርቶችን በማስቀረትና የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ውጤት የታየበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።በ2016 ዓ/ም ከቦታ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ የገለጹት ሀላፊው ከስልጠናና ከብድር ጋር ያሉ ችግሮችንም በመፍታት የዘርፉን ውጤታማነት እናረጋግጣለን ብለዋል።የኤግዚቢሽንና ባዛሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በዚህ ቦታ መሳተፋቸው የገበያ ትስስር ከመፍጠር አኳያ የተሻለ እድል እንደሚፈጥር ገልጸው ለዘርፉ ተግዳሮት ያሏቸውን ከቦታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችንም አቅርበዋል።መጨረሻም የኤግዚቢሽንና ባዛሩን የተመለከተ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።በቀረበ ሰነድ መነሻ ውይይት ተደርጎበታል። ሴነ 13/2015 ዓ.ም ሀዋሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Language »