ከውጭ ያለውን ጠላታችን ከማሸነፋችን በፊት ከውስጣችን ያለውን ቂም እና ጥላቻ ማስወገድ ይገባል-ጠ/ሚ ዐቢይ



ከውጭ ያለውን ጠላታችን ከማሸነፋችን በፊት ከውስጣችን ያለውን ቂም እና ጥላቻ ማስወገድ ይገባል-ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በጆሐንስበርግ ከተማ ኢምፔሪያል ዎንደረርስ ክሪኬት ስታዲየም በመገኘት በሀገሪቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውን ዜጎች ጉዳይ ዙሪያ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር መምከራቸውን ተናግረዋል።

በውይይታቸውም ኢትዮጵያውያን ዜጎች በሀገሪቱ ሁለንተናዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን አብስረዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚደርስባቸውን ችግር ለመፍታት የሀገሪቱ መንግስት አበረታች ምላሽ መስጠቱን ነው የገለጹት።

በዚህ መሰረትም የሀገሪቱ መንግስት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በኩል ኮሚቴ አቋቁሞ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርስን ማንኛውም ችግር በማጣራት እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብተዋል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር አስተባባሪነት የኮሚዩኒቲ ተወካዮች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር እንዲወያዩ ቀጠሮ መያዙን ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪከ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በላባቸው ሰርተው የሚያድሩር ጠንካራ እና ሀገር ወዳድ ዜጎች መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፥ይህ ምግባራቸው በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዘንድ የሚታወቅ መሆኑንም አንስተዋል።

በሀገሪቱ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት የዳያስፖራ ማህበር በዜጎች አንድነት፣ መተሳሰብ እንዲሁም መተባበር ዙሪያ የሚያከናውነወን ተግባር አድንቀው፣ለሌሎች ሀገራት ዳያስፖራዎች አርኣያ እንደሚሆንም አውስተዋል።

የይቅርታ እና የሰላም አባት በሆነችው ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዜጎች ዘረኝነትን በመቃወም በአንድነት እና በመተሳሰብ ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከበርካታ ሀገራት በላይ ገናና ታሪክ የነበራት መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ካለፉት ታሪኮች ተሞክሮ በመውሰድ ሀገሪቱን ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም ከውጭ ያለውን ጠላታችን ከማሸነፋችን በፊት ከውስጣችን ያለውን ቂም እና ጥላቻ ማስወገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታጋይ እና የሀገሪቱ የመጀመሪያ ጥቁር ፕሬዚዳንት የሆኑትን ኔልሰን ማንዴላን በመቀበል እና ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት እገዛ ማድረጓንም አውስተዋል።

(FBC)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Language »