የፊት ጭምብል በ500 ብር እንሸጣለን በማለት ሲያስተዋውቁ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ ከተማ የፊት ጭምብል (ማስክ) በ500 ብር እንሸጣለን በማለት ሲያስተዋውቁ የተገኙ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአራዳ ከፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የወንጀል መርማሪ ምክትል ሳጅን አዳነኝ አዱኛ ተጠርጣሪዎቹ በማህበራዊ ትስስር ገጽ /ፌስ ቡክ/ በተጋነነ ዋጋ ጭምብል እንሸጣለን በሚል በለጠፉት ማስታወቂያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ልዩ ስሙ ገተር ህንጻ አካባቢ ህገ ወጥ መድሃኒቶችን ለመድሃኒት ማስቀመጫና መሸጫ በተከለከለ ቦታ ይዘው መገኘታቸውንም መርማሪው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ከከተማ አስተዳደሩ ግብረ ኃይል ጋር በቦታው ተገኝቶ ለማረጋገጥ ሞክሯል።

ነገር ግን በወቅቱ ጭምብሉ ተሸጦ እንዳለቀና ሌሎች መድሃኒቶች እንዳሏቸው የገለጹላቸው ሲሆን ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠ መድሃኒት በግለሰቦቹ መጋዘን ውስጥ ተገኝቷልም ነው ያለው።

ግለሰቦቹ ጭምብሉን በተጋነነ ዋጋ ከመሸጥ ባለፈ ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠና የጸጉር ማሳደጊያ ነው የተባለ መድሃኒት በ3 ሺህ ብር ሲሸጡ መገኘታቸውም ተገልጿል።

በተጨማሪም በመርካቶ በርበሬ ተራ በበርበሬ ዋጋ ላይ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

በዚህም አንድ ኪሎ በርበሬ ከ130 እስከ 145 ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሱቆች ታሽገዋል።

ነጋዴዎቹ የዋጋ ጭማሪው በርበሬውን ከሚያመጡበት ስፍራ የተደረገ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በቀጣይም በሌሎች ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።

FBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Language »