ከ1 ሺህ 300 ሲ ሲ በታች በሆኑ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የታክስ መጠን ወደ 5 በመቶ እንዲቀንስ ተደረገ



ማሻሻያ በተደረገበት ረቂቅ የኤክሳይዝ ታክስ በአዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለውን የታክስ መጠን ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ እንዲቀንስ ተደረገ።

የገንዘብ ሚኒስቴር በተሻሻለው የኤክሳይዝ ታክስ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በተሻሻለው ረቂቅ ከ1 ሺህ 300 ሲሲ በታች ባሉ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የታክስ መጠን ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ መውረዱን ገልጸዋል።

ይህም የተሽከርካሪዎችን ዋጋ እስከ 83 በመቶ ይቀንሰዋል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በሲጋራ እና አልኮል መጠጥ ላይ እንዲጣል የቀረበው ሃሳብ አነስተኛ ነው የሚል አስተያየት መቅረቡን ጠቅሰው፥ የመጠጥ ኢንዱስትሪው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲጋራ ላይ ብቻ ማስተካከያ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዚህም በሲጋራ ላይ ተጥሎ የነበረው የ35 በመቶ ታክስ ወደ 36 በመቶ ከፍ እንዲል በማሻሻያው መቅረቡን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም በማሻሻያው በታሸጉ የውሃ ምርቶች ላይ ሊጣል የነበረው የ15 በመቶ ታክስ 10 በመቶ ሆኖ መቅረቡንም ነው የተናገሩት።

አምራቾች የውሃ ፕላስቲኮችን የመሰብሰብና አካባቢን እንዳይበክሉ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው ማለታቸው ለማሻሻያው ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የቀረበውን ረቂቅ ማሻሻያ ተመልክቶ በቅርቡ ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትር ዲኤታው አንስተዋል።

ይህን መሰረት በማድረግ በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ ታክስ የተጣለ በማስመሰል የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እስከመውሰድ የደረሰ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

Sources FBC

Language »