አራት ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ በመያዝ ተጠርጥረው በለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን መንግስት ገለፀ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሰጡት መግለጫ እነዚህ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበሩ አራት ኢትዮጵያውያን የሰውነታቸው የሙቀት መጠን ከፍ በማለቱ በጥርጣሬ በቡሌ ጣፋ ኳረንቲን ተለይተው ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እስካሁን በበሽታው የተያዘ ሰው አለመኖሩን ያስታወቁት ተቋማቱ ነገር ግን ከቻይና ውሃን (Wuhan) ግዛት ካለው ዩኒቨርሲቲ የመጡ 4 ተማሪዎች መካከል አንዱ የጉንፋን መሰል ምልክቶች የታዩበት በመሆኑ ሌሎቹንም ሶሰት ተማሪዎች አብረው የመጡ በመሆናቸው በለይቶ ማቆያ ማእከል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ ብለዋል።
ለአራቱም ተጠርጣሪዎች የላቦራቶሪ ናሙና ተሰርቶ ለጉንፋን መሰል በሽታ ነጋቲቭ መሆናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም ለከፍተኛ ምርመራ የደም ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኳልም ነው ያሉት።
አራተኛው ተጠርጣሪ የጉንፋን መሰል ምልክት ያሳየ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት የሁሉም ተጠርጣሪዎች የጤና ሁኔታ ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ከቻይና ጓንዡ ግዛት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሁለት ቻይናውያን መኖራቸውን የቻይና ኤምባሲ ባደረገው ጥቆማ መሰረት ተጓዦቹ በአውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የምርመራ ቦታ ለሁለት ሰዓታት አስፍላጊው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ቫይረሱ ካለበት አካባቢ ጋር ምንም ግንኙነት የለላቸውና በሙቀት ልየታ መሳሪያውም የተገኘ ምልክት ስለሌለ ወደ አገራቸው በሰላም የተመለሱ መሆናቸውን ገልዋል።
ቦቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ያለውን የምርመራ ስራ በተመለከተ የተጓዦች የጉዞ መረጃና ከማን ጋር እንደተገናኙ የሚያሳይ መረጃ በመሰብሰብ የምርመራ ስራው እየተካሄደ እንደሆነና፥ ለዚህ ስራ በሶስት ፈረቃ ተጨማሪ ባለሙያዎች ተመድበው እየተከታተሉት እንደሚገኙም አስታውቋል።
እየተደረገ ባለው ምርመራ ላይ ጥንቃቄ እና ትኩረት ከማድረግ አንጻር ከአየር መንገድ እና ከተለያዩ ኤምባሲዎች ጋር የመረጃ ልውውጥ እና በጋራ የመስራት ስራው ተጠናክሮ እንደቀጠለና በኢትጵያ በሚገኙ አለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያዎች የእስክሪኒግ ስራ ለመጀመር ዝግጅቶች ማጠናቀቃቸውን ነው የገለፁት።
FBC