በኢትዮጵያ ተጨማሪ 3 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተገለጸ

በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በዛሬው ዕለት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ያለበት የመጀመሪያው ሰው ከተገኘ በኋላ ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች ሲከታተል መቆየቱን አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው 117 ሰዎች ተለይተው የቅርብ ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ቫይረሱን ለመለየት የሚያስችል ምርመራ ለማድረግ ከግለሰቦቹ ናሙና እየተወሰደ መሆኑ ተመላክቷል።

ከእነዚህ ምርመራ ከተደረገላቸው እና ከመጀመሪያው ተጠቂ ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ ከነበራቸው ሰዎች መካከልም ሶስት ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥም ሁለቱ የ44 እና የ47 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የጃፓን ዜጎች ሲሆን፥ አንደኛው ደግሞ የ42 ዓመት ኢትዮጵያዊ መሆኑ ታውቋል።

ሁሉም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚሰሩ እና ቫይረሱ ከተገኘበት የመጀመሪያው ግለሰብ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው መሆኑም ተመላክቷል።

በአሁኑ ስዓት የመጀመሪያው ታማሚ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ በለይቶ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የህክምና ክትትል እየተደረገለት መሆኑ ተገልጿል።

FBC

Language »