የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የ6 ወር ግምገማ እየተካሄደ ነው


የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የስድስት ወር አፈፃፀም ግምገማ በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ነው።

በግምገማ መድረኩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

በስድስት ወር አፈፃፀም ግምገማ መድረኩ ላይ የገጠር፣ የከተማ እና የማህበራዊ ክላስተር ዘርፎች አፈፃፀም ሪፖርት የሚደመጥ መሆኑን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

እንዲሁም የተገኙ ጥንካሬዎችን እና ክፍተቶችን በመለየት ለቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም መረጃው ያመለክታል።

በመድረኩ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ፥ የገጠር ሴክተር መስሪያ ቤቶች የስድስት ወር አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም የአርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸውን፣ ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ ከተሰሩ ስራዎች ውስጥም አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች ተጠቅሞ የሚፈልገውን ምርት እንዲያገኝ ለማድረግ ሰፋፊ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ግብርናን ከዝናብ ጠባቂነት ለማላቀቅ በመስኖ ልማት ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን እና በመስኖ ልማት ዙሪያ በክልል እና በፌዴራል መንግስት ደረጃ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

አርሶ አደሩን እና አርብቶ አደሩን ወደ ኢንቨስትመንት ለማሸጋገርም ባለፉት ስድስት ወራት የፋይናንስ እና የብድር ስርዓት በመዘርጋት ስራ ላይ መዋሉን እንዲሁም የገበያ ትስስር የመፍጠር ስራዎች መሰራታቸውን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።

FBC

Language »