የገናሌ ዳዋ III ኃይል ማመንጫ ተመረቀ


የገናሌ ዳዋ III የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ በዛሬው እለት ተመረቀ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የጀርመነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም ብለን ነበር፤ የዛሬው የገናሌ ዳዋ III የውሃ ኃይል ማመንጫ ምረቃ የዚህ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል።

ግድቡ በመመረቁ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም ለባሌ እና ጉጂ ዞን ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

በዛሬው እለት የተመረቀው ግድብ ከኃይል ማመንጨት በተጨማሪ በመስኖ ልማት በርካቶችን የመመገብ አቅም አለው ሲሉም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አክለውም፥ ሀይል ወሳኝ ፍላጎታችን ነው፤ ይህንን ለማሳካት የሚመለከታቸው ተቋማት ለሚሰሩት ስራ መንግስት በቅርበት አመራር ይሰጣል ሲሉም ተናግረዋል።

አሁን የተሰራውን መመረቅ ብቻ ሳይሆን ትኩረታችን የገናሌ ዳዋ ስድስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብን እንዴት መጀመር እና መጨረስ አለብን የሚለው ላይ መሆን አለበት በማለት አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገናሌ ዳዋ ስድስት ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያላነሰ ወጪን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

በግድቡ ልማት ላይ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል፤ ነገር ግን መንግስት ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር የማልማት ፍላጎት እንዳለው ጠቁመዋል።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ከመንግስት ጋር በመሆን በሽርክና የገናሌ ዳዋ ስድስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብን እንዲያለሙ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ለውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲያሳውቁም ገልፀዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሀይል ተደራሽነት ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች ያሉ ሲሆን፥ ይህንን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀይል ተደራሽ የሆነው 45 በመቶ ለሚሆነው ብቻ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በዛሬው እለት የተመረቀውም ይህንን በማሻሻል ረገድ የራሱን ድርሻ እንዳለውም አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ በታዳሽ ሀይሎች ላይ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመግለፅ በተለይም በተፋሰሶች ላይ የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 4 ሺህ 400 ሜጋ ዋት እያመረተች መሆኑን በማንሳት፥ በቀጣይም የህዳሴ ግድብና ኮይሻን ጨምሮ ከሌሎች ታዳሽ ሀይሎች 7 ሺህ 300 ሜጋ ዋት ለማምረት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የህዳሴ ግድብ በቀጣይ ዓመት መጨረሻ ላይ በሁለቱ ተርባይኖቹ ሀይል ማመንጨት እንዲጀምር እንዲሁም በ2015 ዓ.ም የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን እና መንግስትም ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግም አያይዘው ጠይቀዋል።

በዛሬው እለት የተመረቀው የገናሌ ዳዋ III የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ 254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑ ተገልጿል።

የገናሌ ዳዋ III የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ 2 ነጥብ 57 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅምም አለው።

የሃይል ማመንጫው የተገነባው ዝናባማ በሆነው በኦሮሚያ ክልል በጉጂና ባሌ ዞንኖች መካከል መሆኑ የማመንጨት አቅሙን ቋሚና የተሻለ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

ለግንባታው 451 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፥ 60 በመቶው ከቻይናው ኤክዚም ባንክ በብድር እንዲሁም ቀሪው 40 በመቶው ደግሞ በመንግስት ወጪ የተሸፈነ ነው።

ፕሮጀክቱ በ4 ዓመት እንዲጠናቀቅ ውል ታስሮ በ2003 ዓ.ም ቢሆንም የግንባታው አካል የሆነ 2 ኪሎ ሜትር ዋሻ ቁፋሮ ወቅት ባጋጠሙ አለቶች እንዲሁም ከካሳ አከፋፈል ጋር መዘግየቱም ተገልጿል።

FBC

Language »