ኢትዮጵያን ጨምሮ ባፈለው ዓመት ኢንተርኔት በመዝጋት የከሰሩ ሃገራት

ባፈለው የፈረንጆቹ ዓመት ኢንተርኔት በመዝጋት የከሰሩ ሃገራትን ዝርዝር ይፋ ያደረገ አንድ ጥናት “ዓለም በዚህ ምክንያት 8 ቢሊዮን ዶላር ከስራለች” ብሏል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ኢንተርኔትን በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የዘጉ ሃገራት ቁጥር ከምን ጊዜውም የላቀ ነው ሲል ኔትብሎክ የተባለው አጥኚ ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ጥናቱ ላይ እንደተጠቀሰው በተለያዩ ሃገራት 122 ጊዜ ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲሆን በጠቅላላ 22 ሺህ ሰዓታትን እነዚህ ሃገራት ያለ ኢንተርኔት አሳልፈዋል ብሏል።

ባለፉት 12 ዓመታት ጥናቱ ውስጥ የተካቱት መንግሥታት በሃገር ደረጃ ወይም በክልል ደረጃ ኢንተርኔትን ሆን ብለው አጥፍተዋል፤ ዋነኛው ዓለማው ደግሞ ተጠቃሚውን ፌስቡክ ከመሳሰሉ ከማህበራዊ ድር አምባዎች ለማገድ ነው።

ድርጅቱ የኢንተርኔት አዘጋግ ሂደቱን በሁለት ይከፍለዋል። አንደኛው ሙሉ በሙሉ የኢንተርኔቱን ባልቦላ መቁረጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማሕበራዊ ድር-አምባዎችን ከጥቅም ውጭ ማድረግ ነው።

ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ትዊተር፣ ዩቲዩብ እና መሰል ድር አምባዎች ቢታገዱም ተጠቃሚዎች ‘ቪፒኤን’ በመጠቀም ሊያገኟቸው ይችላሉ።

ጥናቱ ይፋ ባደረገው መሠረት አብዛኛዎች የኢንተርኔት መቋረጦች ከተቃውሞ እና አለመረጋጋት እንዲሁም ምርጫ ጋር የተያያዙ ናቸው። የባልቦላው መዘጋት በተለይ ‘በደሃ’ ሃገራት በልማዳዊው ገበያ ላይ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቱ ደርሶበታል። ይህ ማለት ጥፋቱ ጥናቱ ላይ ከተቀመጠው በላይ ሊሆንም ይችላል ማለት ነው።

የኢንተርኔት መዘጋቱ የሰው ልጅ የመናገር ነፃነትን የሚገፍ ነው የሚለው ድርጅቱ ኢንተርኔት መዝጋቱ ለበለጠ አመፅ እንደጋበዘ ታዝቤያለሁ ይላል።

በዚህ ረገድ መካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪቃ ኢንተርኔት በመዝጋት የሚስተካከላቸው አልተገኝም። ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት ደግሞ ተከታዩን ደረጃ ይእዛሉ። እስያ በሶስተኛ ደረጃ የምትገኝ ሲሆን የደቡብ አሜሪካ ሃገራት በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ድርጅቱ ኢንተርኔት የዘጉ ሃገራትን ዝርዝር፤ ያጡትን ገንዘብ [በዶላር] እንዲሁም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከዚህ እንደሚከተለው አስቀምጧል።

ደረጃየሃገራቱ ስም ዝርዝርየከሰሩት ገንዘብ [በዶላር]የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር
1ኢራቅ2.3 ቢሊዮን18.8 ሚሊዮን
2ሱዳን1.8 ቢሊዮን12.5 ሚሊዮን
3ሕንድ [የተወሰኑ ቦታዎች]1.3 ቢሊዮን8.4 ሚሊዮን
4ቬንዝዌላ1 ቢሊዮን20.7 ሚሊዮን
5ኢራን611 ሚሊዮን49 ሚሊዮን
6አልጄሪያ200 ሚሊዮን19.7 ሚሊዮን
7ኢንዶኔዥያ188 ሚሊዮን29.4 ሚሊዮን
8ቻድ125 ሚሊዮን1 ሚሊዮን
9ስሪ ላንካ84 ሚሊዮን7.1 ሚሊዮን
10ምያንማር [የተወሰኑ ቦታዎች]75 ሚሊዮን100 ሺህ
11ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ61 ሚሊዮን7 ሚሊዮን
12ኢትዮጵያ57 ሚሊዮን [1.8 ቢሊዮን ብር]19.5 ሚሊዮን



ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ኢንተርኔቷን ለ274 ሰዓታት ዘግታለች። በተለይ ወርሃ ሰኔ ላይ [አማራ ክልል እና አዲስ አበባ ላይ ከተከሰተው የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ] ኢንተርኔት በሃገሪቱ ለተወሰኑ ቀናት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ነበር።

ከዚያ ባለፈ ሃገር አቀፍ የተማሪዎች ፈተና በሚኖርበት ወቅት ኢንተርኔት በበርካታ የሃገሪቱ ክፍሎች ተቋርጧል። ነገር ግን ኢንተርኔቱን የሚያስተዳድረው ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ መንገሥት ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም።

ከሃገር አቀፍ የኢንተርኔት መቋረጦች ባለፈ በተመረጡ አካባቢዎችም ተጠቃሚዎች ለቀናት ከኢንተርኔት ጋር ተቆራርጠው ቆይተዋል። ይህም ኢትዮጵያን ባላፈው ዓመት ብቻ 2 ቢሊዮን ብር ገደማ አሳጥቷታል።

BBC Amharic

Language »