የከተራ በዓል በዛሬው ዕለት በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ይገኛል።
በመላ ሀገሪቱ ታቦታት ከአድባራት ወጥተው በካህናት፣ በዲያቆናት እና በምዕመናን ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህሩ በመውረድ ላይ ይገኛሉ።
ታቦታት ወደ ማደሪያቸው ጥምቀተ ባህር ከደረሱ በኋላም አዳራቸውን በዚያው የሚያደርጉ ሲሆን፥ በካህናትና ዲያቆናት ዝማሬና ሌሎች ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ይከወናሉ።
ነገ በማግስቱ ደግሞ የጥምቀት በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች የሚከበር ይሆናል።
በዓሉ በአዲስ አበባ በጃን ሜዳ በአቅራቢያ የሚገኙ የ11 ደብራትና ገዳማት ታቦታት የጥምቀት በዓልን በጋራ የሚያከብሩ ሲሆን፥ ዛሬ ከቀኑ ስምንተ ሰዓት ጀመሮ ከአድባራትና ገዳማት ጉዞ በመጀመር ታቦታቱ ምሽት ላይ ጃን ሜዳ ያርፋሉ።
በጎንደር ከተማ ደግሞ የእምነቱ ተከታዮችን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ጎብኝዎች በተገኙበት በደማቅ ስነ ስርዓት መከበር የጀመረ ሲሆን፥ በአሁኑ ሰዓት ታቦታት ከመንበራቸው ወደ ማደሪያቸው ጉዞ ጀምረዋል።
የከተራና የጥምቀት በዓላት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና የአደባባይ በዓላት መካከል ይጠቀሳሉ።