50 ዓመታት የዘለቀው እና ዛረም ድረስ እያመሰን ያለው የብሔር ፖሌቲካ

ከ1960ዎቹ  የንጉሱ ማብቂያና የደርግ ጅማሬ አንስቶ በኢትዮጵያ የተስፋፋው የብሔር ፖሌቲካ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ዘርፌ ብዙ ችግሮች እንደዳረጋት እየሆኑ ያሉ ነገሮች ግልጽ ምስክር ናቸው፡፡ ይህን በስፋት ከማየታችን በፊት እስኪ ለምከተሉት ጥያቀዎች መልስ እንስጥ፡-

  1. ለመሆኑ ቋንቋን መጠቀም  ማንነትን ማወቅ እና የከፋፍለህ ግዛ መርህ አንድ ናቸው?
  2. ህወሓት/ኢህአዴግ በቋንቋና በማንነት ስም ሀገሪቷንና ህዝቦቿን ማከፋፈል ለምን አስፈለገው?
  3. ኢህአዴግ እስከ አሁን እና ለቀጣዮቹ 50/100 ዓመታት ኢትዮጵን ገዝቶ ብሆን ኢትዮጵያ ምን ትሆን ነበር?
  4. አሁን በየአከባቢው የልማት እና የመልካም አስተዳር   ጸር የሆኑ ነገሮች የዚህ ውጠት አይደሉም ብላችሁ ታስባላችሁ?

እንዲህ እያልን ብዙ ጥያቀዎች መጠየቅ ብንችልም እስኪ እነዚህን ጥያቄዎች ለጊዘው እንያቸው፡

በመሰረቱ ማንነትን ማወቅና በራስ ቋንቋ መጠቀም በምንም መስፈርት ከከፋለህ ግዛ መርህ ጋር አንድ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የከፋፍለህ ግዛ መርህ በቅኝ ገዢዎች የተፈጠረ እና ቅኝ ገዢዎች አላማቸው የሚገዟቸውን አገሮች ሀብት እና ጉልበት መበዝበዝ ስለነበር ለዚህ እንዲመቻቸው የፈጠሩት የአጋዛዝ ስልት ነው፡፡ ነገር ግን አንድን የራሱን ሀገር ከሚስተዳድር የፖሊቲካ ድርጅት ይህ በፍጹም አይጠበቅም ነበር፡፡ በመሆኑም  ይህ ለምን ሆኔ የሚለውን ጥያቄ ስንጠይቅ መልሳችን የሚሆነው ኢህአደግ አላማው የነበረው ኢትዮጵያን ማበልጸግና ካለችበት ችግር ማውጣት ሳይሆን የኢትዮጵያን ሀብት በመመበዝበር እና በመዝረፍ የስልጣኔ መሰረት ናቸው የሚላቸውን እና ደጋፊዎቻቸውን የበላይነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ ለዚህም ከስራና ከፈጠራ ውጪ በሙስና የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት በእጁ ስያስገባ የረጅም ጊዜ ጠቃሚ ራዕይ ስላልነበረው በስልጣን መባለግ ጀመረ፡፡ የራሴ የሚላቸውን ሰዎች በየመዋቅሩ በማስገባት ሀገር የመዝረፍ ስራውን አፋፋመው፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ብልግናውን እና ብልሹ አሰራሩን ስረዳው ከስልጣኑ አባረረው፡፡ ነገር ግን ማንነትን ማወቅና በራስ ቋንቋ መጠቀም ተፈጥሮአዊ እና ሰባዊ መብቶች ሰለሆኑ ለከፋፍለህ ግዛ መርህ ጥቅም ላይ መዋል አልነበረባቸውም፡፡ ለዚህም ከኢትዮጵያ ቀድመው ይህን መብት ያረጋገጡ እንደ ህንድ እና ናይጀሪያ ያሉ ሀገራት ትልቅ ምስክር ናቸው፡፡ ህንድ በተለይ በውስጧ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገርባትና ህዝቦቿ ሀገራቸውን በመውደድ የሚታወቁ ሀገር ናት፡፡ እኛ ሀገር ግን ማንነትና የራስ ቋንቋን መጠቀም ለዕኩይ አላማ የዋለ በመሆኑ በሀገሪቱ የኩራት ምንጭ የነበሩ ጠንክሮ መስራትና መማር የተዋረዱበት  እንድሁም የእፍረት ምንጭ የነበሩ መስረቅና መውደቅ ጠናማ ባህሪ የሆኑበት ስራት ፈጥረው ነበር ኢህአደጎች፡፡ሆኖም ግን እኩይ አላማቸው በአጭሩ ተቀጭቷል፡፡

ወደ ሁለተኛው ጥያቀዬ ስመጣ ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሀገሪቱን ህዝቦች በመብት ስም በቋንቋ እና በጎሳ ያከፋፈለበት ምክንያት፡ ካላይ እንደገልጽኩላችሁ ሀገራዊ ማንነቱን የካደ እና በስልጣን እና በራሱ ጎሳ የበላይነት የሰከረ ስለነበር እና ጠንካራ እና አንድ የሆነ ህዝብ የማስተዳር አቅምም ራዕይም ስልነበረው ህዝቡን ማከፋፈል እና አቅሙን ማሳጣት ነበረበት፡፡ ከዚያም እንደ ቅኝ ገዣዎች የተከፋፈሉ እና አቅም የለላቸው ዘጎች እንደ ፈለገ ረግጦ በመግዛት የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፍ ዕኩይ አላማውን ለማሳካት ይህንን ስልት ተጠቅሟል ባይ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያዊያን ጠላታቸውን እና ወዳጃቸውን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር እና የሆነውን አድርገዋል፡፡

ወደ ሦስተኛው ጥያቄየ ስመጣ ኢሕአደግ በስልጣን ቆይቶ ብሆንና ሌላ 50 እና 100 ዓመታት ገዝቶ ብሆን ኖሮ ብዙ የማይመቹ ሁኔታዎች ይፈጠሩ ነበር፡፡ ለዚህም የትምህርት ስራቱ የፈረሰበት ሁኔታ ብዙ ምስቅልቅል የወጡ ነገሮች እንደምፈጠሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በዚህም ሀገሪቱ በስም ያለች ነገር ግን በተግባር የፈረሰች ሀገር ትሆን ነበር፡፡ ፈጣሪ ምስጋና ይግባውና በጊዜ ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ በለውጥ ሀይሎች ተወግደዋል፡፡

ወደ አራተኛውና ወደ መጨረሻ ጥያቄዬ ስገባ በኢትዮጵያ በየክልሉ እና በየሰፈሩ ያሉት ብዙ ችግሮች የሕወሓት/ኢህአዴግ የ27 ዓመታት አገዛዝ የፈጠራቸውና የቀበራቸው ፈንጂዎች ውጠት ናቸው፡፡ ስለዚህ አነኝህን ችግሮች ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት ወደ ምለው ስወስዳችሁ፡ በፖሊሲ የተደገፈ ችግሮቹን የሚፈታ እርምጃ በመንግስት በኩል መወሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡ በተለይ ወጣቱ በኮታ ሹመት እና በሙስና ዘላቂ ሲከት እንደማይመጣ ተረድቶ ጠንክሮ መማር ብዛሃ ቋንቋና ብዛሃ ባህል የሚዎድ ለችግሮች መፍትሄ ለማምጣት የሚተጋ ሀገሩን እና የሀገሩን መንግስት የሚያከብር ችግሮች ስኖሩ በሰላማዊ መንገድ እና በሀሳብ የበላይነት የሚታገል እንድሆን ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ ባጠቃላይ ይህ በሀገራችን ላሉ ችግሮችን በጥያቄ መልክ ያነሳሁትና ምላሽ ለመስጠት የሞከርኩበት እና መፍትሄ ይሆናሉ ብዮ ያስቀምትኩት የግሌ ሀሳብ ስሆን እናንተም ሀሳባችሁን እንድታካፍሉ እየጋበዝኩ ሀሳበን ስላነበባችሁ እያመሰገንኩ በሌላ ሀሳብ እስክንገናኝ ሰላማችሁ ይብዛ እላለሁ፡፡

ጥቅምት 08/2019 ዓ/ም አዲስ አበባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Language »